Jump to content

ጓሳ

ከውክፔዲያ
ጓሳ

ጓሳ ወይም በደኔ ወይም ጀሞ (Balanites aegyptiaca) ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ዛፍ ነው።

የተክሉ ሳይንሳዊ ጸባይ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እስከ 10 ሜትር ድረስ የሚቆም ቀጭን ዛፍ ነው። ለቅርንጫፎቹ ረጅም፣ ቀጥ ያሉ ዐረንጓዴ እሾሆች በጥምዝምዝ አሉባቸው። ከእሾሆቹ መሠረት ጨለማ-አረንጓዴ ውሁድ ቅጠሎች ይበቅላሉ፣ ውሁዱም ቅጠል ከ፪ ቅጠሊቶች እየሆነ በቅርጽም ሆነ በስፋት ሊለያዩ ይችላሉ። ሽንሽን ግንዱ ግራጫማ-ቡኒ ሻካራ ልጥ አለው፤ ይህም በረገፈበት ቦታ ቢጫ-አረንጓዴ እራፊ ይኖረዋል።

ህብረአበባው የጥቂት አበቦች ዘለላ ሲሆን አበቦቹም ወይም ዘንግ-አልባ ወይም በአጭር አገዳ ላይ የሚቀመጡ ናቸው። የአበባው እንቡጥ ሞላላ እና በጉርምስና ሥሥ ጽጉር ያለበት ነው። አበቦቹ አረንጓዴ-ቢጫ ቀለም፣ ፍናፍንታም ጾታ፣ አምስት ቅጠል በክቦሽ ምጥጥን ያላቸው ናቸው፤ የአበባ ቅጠሎች 8-14 ሚሊሜትር ባጋማሽ ናቸው። የኅብራበባ ስሪት ግራጫማ ቀለም፣ ለሥላሣ ጽጉር ያለው፣ ከ10 ሚሊሜትር ያልረዘመ ነው። ሞልሟላ ፍሬው በተለምዶ ከ4 ሴንቲ ሜትር ያልረዘመ ነው፣ ያልበሰለ ሲሆን አረንጓዴ ነው፣ ሲበሰልም ቡናማ ይሆናል፣ ከሽካሽ ቆዳው ዝልግልግ ቡናማ ልጥልጥ አለበት፣ ይህም ጽኑ ፍሬ ድንጋይ አለበት።

አናጢ ጉንዳን Camponotos sericius ከአበባው ከሚንቆረቆር ወለላ ይመገባል። የጥቅል ጎመን ዛፍ ንጉሥ ብል (Bunaea alcinoe) ኤጭ ዛፉን ርግፈ ቅጠል ያደርገዋል።

በብዛት የሚገኝበት መልክዓ ምድር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዛፉ በአፍሪካ በኩል ይገኛል።

የተክሉ ጥቅም

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ጓሳ በግብጽ ቢያንስ ለ4,000 ዓመታት ታርሷል። ከ2000 ዓክልብ. በመቃብሮቹ ውስጥ የፍሬው ድንጋይ እንደ ስለት እቃ ተገኝቷልና። ዘሩ ያለበት ብጫው ፍሬ መራራ ቢሆንም ሊበላ ይችላል። ዝሆን ቢያገኘው ይበላዋል። በተረፈ እንደ ረሃብ ምግብ ያገልግላል፤ ቅጠሉም አበባም በሰዎች ሊበሉ ይቻላል፤ ዘይታም ዘሩ መራራነቱ እንዲቀነስ ይፈላል፤ ከማሽላ ጋር ይበላል። በደረቅ ወራት ቢሆንም ፍሬውን ስለሚያስገኝ፣ ለበረሃ ምድሮች ዋጋ ያለው ዛፍ ይቆጠራል። ፍሬውም ለአረቄ ሊቦካ ይቻላል።

እመጫቶች ፍሬውን በአጥሚት ይበሉታል፤ ዘይቱ ማጋቱን ያሻሽላል። ዘይቱ ደግሞ ለራስ ምታት ያሻሽላል።

ዘይቱ ከወጣ በኋላ የተረፈው ዘር ቂጣ በአፍሪካ በተለምዶ ለመኖ ይጠቅማል።

የጓሳ ዘር፣ ፍሬ፣ እና የልጥ ውጥ ቢልሃርዝያን ወዘተ. የሚፈጥሩትን ቀንድ አውጣዎችና ትሎች ይገድላል። የትል፣ የጉበት ወይም የጣፊያ ችግሮች እንዲህም ይታከማሉ። በምዕራብ አፍሪካ ባህላዊ መድሃኒት፣ የልጡ ውጥ ደግሞ ለፍላጻ መርዝ የሚሽር መድሃኒት የጠቅማል።

ዛፉ ናይትሮጅን ቅንበራ ያደርጋል። ቡናማ-ቢጫው እንጨቱ እቃ ለመሥራት ይስማማል፤ ለማገዶ ብዙ ባለማጤሱ መልካም ነው፣ ለከሰልም ጥሩ ነው። ልጡም ጭረት ይሰጣል፣ የቅርንጫፎች ሙጫ ለማጣበቂያ ያገልግላል፤ ጽኑ ዘሮችም ለዶቃ ወይንም ለጌጥ ተጥቅመዋል።

አፍሪካ ሳህል የሚኖሩ ነገዶች እሾሁን በንቅሳት ይጠቅማሉ።