Jump to content

የሕገ መንግሥት ታሪክ

ከውክፔዲያ

ሱመር ከተማ ላጋሽ አለቃ ኡሩካጊና በ2093 ዓክልበ. ያሕል ያዋጀ ሕገ ፍትሕ በታሪካዊ መዝገብ እስከምናውቀው ድረስ መጀመርያ የሕገ መንግሥት ሰነድ ነው። ሰነዱ እራሱ ገና አልተገኘም፤ ነገር ግን ለዜጎቹ አንዳንድ መብት እንደ ፈቀደላቸው ይታወቃል። ለምሳሌ ለመበለትና ለደሀ አደጎች ቀረጥ እንዳስቀረላቸው ድሆችንም ከሃብታሞች አራጣ እንደጠበቃቸው ይታወቃል።

ከዚህ በኋላ ብዙ መንግሥታት በተጻፈ ሕግ እንዲገዙ ልዩ ስርዓት ነበራቸው። ከተገኙት ሕግጋት ሁሉ ጥንታዊ የሆነው በ1983 ዓክልበ. የገዙ የኡር ንጉሥ የኡር-ናሙ ሕግጋት ነው። በተለይ ዕውቅ የሆኑ የጥንት መንግሥት ሕጎች የኢሲን ንጉሥ ሊፒት-እሽታር ሕግጋት (1832 ዓክልበ.) ፤ የኤሽኑና ሕግጋት (ምናልባት 1775 ዓክልበ. ግድም)፤ የባቢሎን ንጉሥ ሃሙራቢ ሕግጋት (1704 ዓክልበ.) እና፤ ሕገ ሙሴእስራኤል (1661 ዓክልበ.) ናቸው። ሕገ ሙሴ በተለይ በኦሪት ዘጸአት 21 እና 22 ያህዌ አስተካክሎ ከነዚህ ሁሉ የተሻሸሉት ብያኔዎች ይጠቅልላል። በኋላ ኬጢያውያን (1488 ዓክልበ. ግድም) እና አሦር (1080 ዓክልበ. ግድም) በበኩላቸው ለራሳቸው ሕግጋት አወጡ።

በ628 ዓክልበ.፣ ድራኮ የሚባል ጸሃፊ የአቴና ከተማ ሕግጋት ጻፈ፤ ይህም ሕግ እጅግ ጨካኝ ሆኖ ይሙት በቃ ለማንኛውም ጥፋት ወሰነ። በ600 ዓክልበ.፣ የአቴና አለቃ ሶሎን አዲስ ሕገ መንግሥት ፈጠረ። የሰራተኞች ሸክም አቀለለ፣ ነገር ግን ባላባትነት በልደት ሳይሆን በንብረት ብዛት እንዲቈጠር አስደረገ። ክሊስቴኔስ እንደገና በ516 ዓክልበ. በዴሞክራሲያዊ መሠረት የተሻሸለ ለአቴና ሕገ መንግሥት አወጣ።

ግሪክ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ በ350 ዓክልበ. ግድም የሕገ መንግሥት ሀሣብ ለይቶ ዐወቀ። በጽሑፎቹ የአቴና፣ የስፓርታና የካርታግና ሕገ መንግሥቶች ያነጻጽራል። በመደምደሚያው የተሻለው ሕገ መንግሥት ከንጉሣዊ፣ ከመኳንንታዊና ከሕዝባዊ ወገኖች የተደባለቀ መሆኑን ገመተ። በሀሣቡ በመንግሥት የሚከፋፈሉ ዜጎች ከማይከፋፈሉ ከባርዮችና ዜጎች ካልሆኑ ሰዎች ልዩነት አደረገ።

ሮማውያን መጀመርያ «12ቱ ሰንተረዦች» የተባለውን ሕገ መንግሥት ያወጡ በ457 ዓክልበ. ነበር። ከዚያ በኋላ አንዳንዴ የተለያዩ ሕጎችና ትእዛዛት ይጨምሩበት ነበር እንጂ እስከ መጽሐፈ ቴዎዶስዮስ ድረስ (430 ዓ.ም.) ሌላ ክምቹ ሕገ መንግሥት አልኖረም ነበር። በኋላም በምሥራቁ መንግሥት (ቢዛንታይን) በኩል መጽሐፈ ዩስጢኒያኖስ (526 ዓ.ም.) ለአውሮፓ ከፍ ያለ ተጽእኖ ነበረው። ይህም በምስራቁ ነገሥታት 3ኛ ሌዎን ኢሳውራዊ «ኤክሎጋ» (732 ዓ.ም.) እና በ1ኛ ባሲሌዎስ «ባሲሊካ» (870 ዓ.ም.) በተባሉት ሕገ ፍትሐን ተከተለ።

ሕንድ ንጉሥ አሾካ መንግሥት የአሾካ አዋጆች ሕግጋት በ264 አክልበ. መሠረቱ።

ከምዕራቡ ሮማ መንግሥት ውድቀት ደግሞ ወደ ተረፈው ሕዋእ ውስጥ ከፈለሱት ጀርመናውያን ወገኖች አብዛኛው የራሳቸውን ሕጎች ዝርዝር በጽሑፍ አወጡ። በተለይ የሚታወቁም የቪዚጎቶች አለቃ ዩሪክ ሕግ (463 ዓ.ም.)፣ የቡርጎንዳውያን ሕግጋት (እኚህ ለጀርመናውያንና ለሮማውያን የተለያየ ፍትሕ ነበራቸው)፣ የአላማናውያን ሕግጋትና፣ የፍራንኮች ሕግጋት ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የተጻፉት ከ492 ዓ.ም. ጀምሮ ነው። በ498 ዓ.ም. የቪዚጎቶች አለቃ 2ኛ አላሪክ መጽሐፈ ቴዎዶስዮስና አንዳንድ የተለያዩ የቀድሞ ሮማ ሐገጋት አከማችተው አዋጁአቸው። ከዚህም በኋላ የታዩ ሕጎች የሎምባርዶች ሕግጋት (635 ዓ.ም.)፣ የቪዚጎቶች አዳዲስ ሕግጋት (646 ዓ.ም.)፣ የአላማናውያን አዳዲስ ሕግጋት (722 ዓ.ም.) እና የፍሪዝያውያን ሕግጋት (777 ዓ.ም.) አሉ። በአውሮፓ አኅጉር ላይ የተጻፉት እነኚህ ፍትሖች ሁሉ በሮማይስጥ ቢጻፉም፣ በእንግሊዝ አገር ግን የተጠቀሙት ሕጎች ከኬንት ንጉሥ ኤጠልቤርት ሕጎች (863 ዓ.ም.) ጀምሮ በጥንታዊ እንግሊዝኛ የተቀነባበሩ ነበሩ። በ885 ዓ.ም. ታላቁ አልፍሬድ ይህንንና ሁለት የድሮ ፍትሖች ከሕገ ሙሴና ከሕገ ወንጌል ጋራ አጋጥመው የእንግሊዝ ሕገ መንግሥት ዶም ቦክ ሠርተዋል።

596 ዓ.ም. በጃፓን 17 አንቀጽ ያለ ሕገ መንግሥትልዑል ሾታኩ እንደተጻፈ ይታመናል። እንዲሁም በ614 ዓ.ም. ከነቢዩ መሐመድ የወጣው የመዲና ሕገ መንግሥት ዕጅግ ጥንታዊ ምሳሌ ነው።

ዌልስ በ940 ዓ.ም. አካባቢ ንጉስ ህወል ዳ ሕጎቹን ጻፉ። በዛሬው ሩሲያ ደግሞ የክዬቭ ታላቅ መስፍን ያሮስላቭ ጥበበኛው ፕራቭዳ ያሮስላቫ የተባለውን ሕገ መንግሥት በ1009 ዓ.ም. ያህል ሠሩ። ይህ ሕግ በ1046 ታድሶ በኪዬቭ ሩስ በሙሉ ህጝ ሆነ።

ስሜን አሜሪካ የኖሩ ኗሪ ጎሣ ሆደነሾኒ 'የአፈ ቃል' ሕገ መንግሥት «ጋያነሸጎዋ» የነበራችው ከ1080-1140 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ሕግ በከፊል ለአሜሪካ ሕገ መንግሥት ተጽእኖ እንደነበረው ይታመናልና የአሜሪካ ምክር ቤት በ1981 ዓ.ም. ይህንን ግንዛቤ አስታወቀ።

እንግሊዝ አገር1092 ዓ.ም. ንጉስ 1 ሄንሪ የነጻነት ሥርአት የተባለውን ሰነድ አዋጀ። ይህ መጀመርያ የንጉሱን ሥልጣን ወሰኖ ንጉሡ ለቤተ ካህናትና ለቤተ መሳፍንት ወገኖች የሚገባውን እንቅብቃቤ ገለጸ። ይህም መሰረት በመኳንንቱ ሲዘረጋ በ1207 ዓ.ም. የእንግሊዝ ንጉሱን ዮሃንስ (ጆን) ማግና ካርታ («ታላቅ ሥርዓት») የሚባለውን ሰነድ እንዲፈርሙት አስገደዱዋቸው። ከዚሁ መሃል ቁም ነገር የሆነው ንጉሡ ያለ ሕጋዊ ሂደት ማንንም ሰው እንዳይገድሉ፣ ከአገር እንዳያሳደዱ፣ ወይም እስር ቤት እንዳያስገቡ ከለከላቸው። በዚያ ወቅት ያ ሰነድ በእንግሊዝ አገር የነጻነት መሠረት ሆነ።

1212 እና 1222 ዓ.ም. መካከል አንድ የሳቅሰን አስተዳዳሪ አይከ ቮን ረፕጎቭ ያቀነባበረው ሕግጋት ሳቅሰንሽፒግል በአንዳንድ ጀርመን ክፍላገር እስከ 1892 ዓ.ም. ድረስ ላይኛ ሕገ መንግሥት ሆነ።

1228 ዓ.ም. ሱንዲያታ ከይታ ማሊ መንግሥትን ለማወሐድ የ'አፈ ቃል' ሕገ መንግሥት አወጡ። ይህ ሕግ 'ኩሩካን ፉጋ' ተብሎ ነበር።

1240 አካባቢ በግብጽ አገር ቅብጡ አቡል ፋዳዒል እብን አል-አሣል ፍትሐ ነገሥትአረብኛ ጻፉ። እብን አል-አሣል ሕጎቹን የወሰዱት በከፊል ከሃዋርያት ጽህፈቶችና ከሕገ ሙሴ፤ በከፊልም ከድሮ ቢዛንታይን ነገስታት ሕጎች ነበር። መጽሐፉ በግዕዝ ተተርጉሞ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ወቅት በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በ1450 አከባቢ እንደነበር የሚል ታሪካዊ መዝገብ አለ። ቢሆንም መጀመርያ እንደ ሕገ ምንግሥት መጠቀሙን የተመዘገበው በዓፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን (ከ1555 ጀምሮ) ነው። ፍትሐ ነገስት እስከ 1923 ዓ.ም. የብሄሩን ዋና ሕግ ሆኖ ቆየ።

1904 ዓ.ም. ዐጼ 2 ምኒልክ የዘመናዊ ሕገ መንግሥት ፅንሰ ሀሳብ ተረድተው በጸሀፊው መምሬ ብስራት አንድ ሕገ መንግሥት የሚመስል ሰነድ ታተመ፤ ይህ ግን በውነት ሕገ መንግሥት አይባልም። «በምኒሊክ ስለተቋቋሙት ሚኒስቴሮች በምሳሌ የቀረበ ጽሑፍ» በምሳሌና በትርጓሜ የእያንዳንዱን ሚኒስቴር ሥራ እንደ ሰውነት አካላት አስመሰለ። ለምሳሌ፦

«የራስ ሥራ - በነፍስና በስጋ ባጥንትና በዥማት ተዋደው በሚኖሩ አካላት ሁሉ አለቃና የውቀት መሰብሰቢያ ሳጥን ነው...
የዦሮ ሥራ - ዦሮ በትምህርት የሚገኘውን ጥበብና ዕውቀት ሁሉ ከራስና ከልብ ለማዋሐድ የድምጽ ኃይል የሚስብ መኪናነት አለው። ዦሮ ባይኖር ዕውቀትና ፍሬ ያለው ንግግር ባልተገኘም ነበር...
ያይን ሥራ - ዓይን ለማየት ከብርሃን ጋራ ተስማምቶ የተፈጠረ ያካላት ሁሉ መብራት ነው። በጅና በግር ለሚሠራ ሥራ በትምህርት ለሚገኝ ጥበብ ሁሉ መሪ ነው። ግዙፍ ሆኖ የተፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ ለማየት ይችላል...
የልብ ሥራ - ልብ የደግና የክፉ ሃሳብ መብቀያ ነው...
የጅ ሥራ - እጅ በጥበብ ለተገኘ ሥራ ሁሉ የብረትና የናስ የወርቅ ፋብሪካና መኪና በያይነቱ፤ የርሻ የጽሀፈት የስፌት የቤት ሥራ በያይነቱ፤ ይህን ለመሰለ ሁሉ ሠራተኛ ነው...
የግር ሥራ - እግር ለነዚህ ለተቆጠሩት ሁሉ መቆሚያ ጉልበትና ብርታት ልብ ወደ አስበበትና ወደ ታዘዘበት መሄጃ ነው...»

የሚመስል ቋንቋ በውስጡ አለበት።

ኢትዮጵያ መጀመርያ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት የተቀበለችው በ1923 አመተ ምኅረት በአጼ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የታወጀ ሲሆን የሕግ አማካሪ ቤቶች በሁለት ያስከፈለ ነው። ይህ የመንግሥታቸው ዋና መሠረት ሆኖ እስከ 1948 አ.ም. አገለገለ፤ በዚያ አመት ተሻሽሎ በወጣ ሕገ መንግሥት ሕዝቦች በመንግሥት ሥራ የሚጫወቱት ሚና እንደገና ተስፋፋ። ይህ ብቻ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሆኖ እስከ 1967 አ.ም. ቆየ፤ የዛኔ በደርግ በግፍ (በሕገ መንግስት እራሱ ባልሆነ ሂደት) ተሰረዘ።