ዎቮካ
ዎቮካ (1848 ዓ.ም. አካባቢ እስከ 1925 ዓ.ም.) ወይም ጃክ ዊልሶን የስሜናዊ ፓዩት ጎሣ ሃይማኖታዊ መሪ ሲሆን «የመንፈስ ጭፈራ» የተባለውን እንቅስቃሴ መስራች ነበረ። የዎቮካ ትርጉም በስሜናዊ ፓዩትኛ 'እንጨት አጥራቢ' ነው።
ዎቮካ በ1848 ዓ.ም. አካባቢ ከካርሶን ሲቲ፣ ኔቫዳ በስተደቡብ-ምሥራቅ በስሚስ ሸለቆ ዙሪያ ተወለደ። የቀደመው ፓዩት ሃይማኖታዊ መሪ ኑሙ-ታይቦ ትምህርት ለዎቮካ ትምህርት ተመሳሳይ ነበረና ይህ ኑሙ-ታይቦ ምናልባት የዎቮካ አባት ነበረ። ምንም ቢሆን፣ ዎቮካ እንደ ባለ መድኃኒት አንዳንድ መልመጃ እንደ ተቀበለ ግልጽ ነው። የዎቮካ አባት በ1862 ዓ.ም. አካባቢ ካረፈ በኋላ፣ ልጁ በዬሪንግተን፣ ነቫዳ ገበሬ ዴቪድ ዊልሶንና በሚስቱ ሜሪ ቤተሠብ ውስጥ ታደገ። ዎቮካ በአቶ ዊልሶን እርሻ ላይ ይሠራና ከነጮች ጋር ስሙን 'ጃክ ዊልሶን' ተባለ። ዴቪድ ዊልሶን ጽኑዕ ክርስቲያን ስለሆነ፣ ዎቮካ በዚያ እየኖረ፣ የክርስትና ትምህርትና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከርሱ ተማረ።
ዎቮካ ኃይለኛ ባለ መድኃኒት እንደ ሆነ ገናኝነት በወጣጥነቱ ቶሎ አገኘ፤ አሁንም ምታት እንዳወቀ ይታመናል። በአልፎ አልፎ ጊዜ አንድ ይሠራ የነበረው ድርጊት በረሽ መተኰሱ ሲሆን ይህ ምናልባት ጥይት ከአየር እንደመያዙ የመሰለ ትርዒት ሊሆን ይችላል። ስለዚሁ ትርዒት የተስፋፋው ወሬ የላኮታ ሕዝብ ጎበዞች 'የመንፈስ ሸሚዝ' ልብስ ቢለብሱ ጥይት ለማቆም እንደ ተቻላቸው ሊያሳምናቸው ችሎታው ነበረው። ዎቮካ ደግሞ ከመሬት የመስፈፍ ትርዒት እንዳሳየ ይባል ነበር። አየሩን ለማሠልጠን ችሎታ እንደያዘ የሚወራው አባባል በፓዩቶች ዘንድ ከሥልጣኑ ምንጮች ዋና ነበረ። ለምሳሌ በሙቀት ወራት የበረዶ ቊራጭ ከሰማይ እንዳወጣ ተባለ።
በ1881 ዓ.ም. በፀሐይ ግርዶሽ መካከል ዎቮካ የትንቢት ራዕይ እንደነበረው አለ። የዎቮካ ራዕይ ስለ ሙታን ትንሣኤ ሲሆን 'ቀይ ሕንዶች' የተባሉ ባህሎች በሙታን ትንሣኤ (በዕለተ ፍትሕ) አገራቸውን (ስሜን አሜሪካ) በምላሽ ይቀብላሉ የሚል ራዕይ ነበረ። የዚያን ጊዜ አገሩ ጎሽና አጋዘን የመላበት ደስተኛ እርሻ መሆኑ እንጂ ምንም እርጅና ወይም በሽታ አለመገኘቱ በዚያ ራዕይ ታየው። በዎቮካ ትምህርት ይህን ራዕይ ለማወቅ ለኗሪ ሕዝቦች የሚያስፈልገው ጽድቅ ተግባር እንዲኖሩ በየስድስቱም ሳምንት የ5 ቀን ጭፈራ እንዲጨፍሩ ነበር። ይህ ጭፈራ 'የመንፈስ ጭፈራ' (Ghost Dance) ይባላል። የዎቮካ ትምህርት በብዙ ኗሪ ጎሣዎች መካከል ተስፋፋ፤ በተለይም በላኮታ ሕዝብ ተስፋፋ።
ዎቮካ የስለማዊነት መልእክት ብቻ አስተማረ፣ ግፍ ግን ጠቃሚ አለመሆኑን አስተማረ። ሆኖም በላኮታዎች መንፈስ ጭፈራ እንቅስቃሴ ዘንድ፣ አንዳንድ ደቀ መዝሙር ነጮቹን ስለመቃወም ያስተምር ነበር። ስለዚህ እነዚህ ጭፈራዎች ብዙ ጭንቀትና ፍርሃት በመንግሥት ባለሥልጣናት ይፈጥሩ ጀመር። ይህ ሁኔታ በዉንደድ ኒ እልቂት (1883 ዓ.ም.) ከፍተኛ ሚና አጫወተ።
በ1884 ዓ.ም. የአንትሮፖሎጂ መምህር ጄምስ ሙኒ ቃለ መጠይቅ ከዎቮካ ጋር አደረገ። በዚህ ቃለ መጠይቅ፣ ዎቮካ ወደ ሌሎቹ ጎሣዎች (ለምሳሌ ወደ ሻየን፣ አራፓሆ) የላከውን መልዕክት አሳየው። በዚህ መልእክት፣ እግዚአብሔር 'መሲሔ ኢየሱስ አሁን በምድር ላይ ነው' ብሎ እንዳሳወቀው ይላል።
ዎቮካ በዬሪንግተን በ1925 ዓ.ም. አረፈና በሹርጽ፣ ኔቫዳ በፓዩት መቃበር ተቀብሯል።